አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ ፤ ከኢትዮጵያውያን ዕውቅ የፊልም ባለሙያዎች ጋር በድንቅ ጥምረት ስራዎችን እያቀረበ የሚገኘው አቦል ቴሌቪዥን ለተመልካቾች እጅግ አስደሳችና ለደንበኞች የሚመጥኑ አዳዲስ ይዘቶችን በብዛት እያደረስ ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት ግዙፍ፣ አዳዲስና እውቅ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማሳተፍ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ታሪክ ፋና ወጊ የሚያድርጉትን ተወዳጅና እለታዊ የሆኑ ተከታታይ ቴሌኖቬላዎችን ማቅረቡና እያቀረበ መሆኑም ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ አነጋጋሪ፣ ልብ አንጠልጣይና በላቀ ጥራትና ሙያዊ ብስለት የተዘጋጀውን “ግዛት” የተሰኘ አዲስ ቴሌኖቬላ ለተመልካቾች ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
“ግዛት” ቴሌኖቬላ ‘The Queen’ከተሰኘው የኤምኔት ተወዳጅ የደቡብ አፍሪካ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ በመነሳት የኢትዮጵያን ወግ፣ ባህል፣ እሴትና የአኗኗር ይትባሃል በጠበቀ ሁኔታ የተዘጋጀ ድራማ ነው፡፡ “ግዛት”በታዋቂዋ የፊልም ባለሙያ ኤደን ጌታቸው ፕሮዲዩስ የተደረገ ሲሆን በቴሌቪዥን ድራማዎች ትወና አንቱታን ያተረፉ ድንቅ ተዋንያን ተሳትፈውበታል። ከእነዚህም መካከል ታምሩ ብርሃኑ፣ ቢኒያም ወርቁ እና ሜሮን እንግዳ ይገኙበታል። “ግዛት” ሌሎችም በማራኪ ትወናቸው ገፀ-ባህሪያትን ሆነው የሚተውኑበትና በአቦል ቴሌቪዥን ለረጅም ጊዜያት በየዕለቱ ከሰኞ እስከ አርብ የሚተላለፍ ቴሌኖቬላ ነው፡፡
ግዛት ልብ እያንጠለጠለ የሁለት ቤተሰቦችን የግዛት ሽኩቻ፣ የገንዘብ ፍቅርና ጥቅም ፍለጋ ብሎም በተለያየ አጋጣሚ በሚፈጠሩ ክስተቶች የቤተሰብ ፍቅር በገንዘብ ሲፈተን የሚያሳይ ሲሆን በየክፍሉ `ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ነው` በሚያስብሉ ድርጊቶች የተሞላ ድንቅ ተከታታይ ድራማ ነው።
በ“ግዛት” የሀረግ ገፀ-ባህሪን ተላብሳ የምትጫወተው ሜሮን እንግዳ ሙሉ ጊዜዋን ለድራማው በማዋል ገፀ-ባህሪዋን ልዩ ውበትና ጉልበት በመስጠት የትወና ብቃቷን ያሳየችበት ሲሆን በሌላ በኩል ታምራት በለጠ ወይም ሰመረ ደግሞ አዲስ ችሎታና ብቃት ለፊልም ኢንዱስትሪው ይዞ የመጣበት ነው። ይህ ተዋናይ ለድራማው እንዲተውን እጩ የሆኖ የቀረበው የቀረፃ ወይም የፕሮዳክሽን አባል ሆኖ እያሰራ ባለበት ወቅት የግዛት ዳይሬክተር ኤደን ጌታቸው እምቅ ችሎታውን ተገንዝባ `ሰመረ`ን ወክሎ እንዲጫወት መርጣዋለች።
የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገሊላ ገ/ሚካኤል “መልቲቾይስ/ዲኤስቲቪ ለሀገር በቀል ይዘቶች መጎልበት ግንባር ቀደም አካል እንደመሆኑ መጠን በሀገር ውስጥ መዝናኛዎች ለደንበኞቻችን ምርጥ ምርጡን እያቀረበ ነው። ተመልካቾቻችንን የሚማርኩና ከዕለተ ዕለት ህይወታቸው ጋር ቀረቤታ ያላቸውን ታሪኮችን በላቀ ጥራት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ የፕሮዳክሽን ቡድን አባላትም ሆኑ የአቦል ቴሌቪዥን ተመልካቾች አስደሳችና ልዩ የመዝናኛ ጊዜን በ“ግዛት” እለታዊና ተከታታይ ቴሌኖቬላ እንደሚያጣጥሙ እምነታችን የጸና ነው’ ብለዋል፡፡
“ግዛት” ከሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በጎጆ ፓኬጅ ዲኤስቲቪ-አቦል ቻናል 465 ከምሽቱ 2:30 መተላለፍ የሚጀምር ሲሆን ተመልካቾች ሊያመልጣቸው የማይገባ ድንቅ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይህንን እና ሌሎችም ተጨማሪ አዝናኝ ሃገርኛ ድራማዎችን በዲኤስቲቪ-አቦል ቻናል በጎጆ ፓኬጅ እንዲከታተሉ ዲኤስቲቪ ያስገቡ ፣ ደንበኝነትዎን ያራዝሙ!